Blog 7. Party Politics (in Amharic) by Dr. Getatchew Haile (2014)

ለዛሬው ድርሰቴ የሰጠሁት ርእስ ሐሳቤን ትንሽ ለወጥ ባለ መንገድ ላቀርብ መነሣቴን ያመለክታል። የጆሯቸው የዕለት እንጀራ “ሰበር ዜና” የሚሉት በአንድ መሥመር ማእድ ላይ የሚቀርብ ትኩስ ወሬ የሆነ ሰዎች አብረውኝ እንደማይዘልቁ እገምታለሁ፤ ግምቴ ቢሳሳት ምንኛ በተደሰትኩ። “ጸዋትው” የ “ጾታ” ብዙ ቍጥር ነው። “ትምክሕተኞች” የምለው አባቶቻቸው በሠሩት የሚያኮራና የሚያስመካ ታሪክ ይህን ቅጽል ያተረፈላቸውን ኢትዮጵያውያንን ነው።

“ጾታ” የሚለው ቃል ሲነሣ፥ ለብዞዎቻችን ትዝ የሚለን የክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ የአማርኛ ሰዋስው ነው። እንደ ብላታ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ሐሳብ አፍላቂዎችና እቃ ፈጣሪዎች ናቸው። ለሚያፈልቋቸው ሐሳቦችና ለሚፈጥሯቸው እቃዎች ስም ያወጡላቸዋል። መዛግብተ ቃላት ቶሎ ቶሎ የሚያረጁት ስለዚህ ነው። ከአሮጌው ይልቅ በቅርብ ጊዜ የታተመውን መዝገበ ቃላት የምንመርጠው ለአዳዲስ ነገሮች የወጡትን አዳዲስ ስሞች (አዲሶቹን ቃሎች ማለት ነው) ቀደም ብለው በታተሙት በአሮጌዎቹ መዛግብተ ቃላት ውስጥ ስለማናገኛቸው ነው።

ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ የመጀመሪያው የአማርኛ ሰዋስው ጸሐፊ ስለነበሩ፥ ሰዋስው ላቀፋቸው ብዙ ሐሳቦች ስም አውጥተውላቸዋል። ለምሳሌ፥ ከላይ “ጸዋትው” የሚለውን ቃል “ብዙ ቍጥር” ያልኩት ከእሳቸው የሰዋስው መጽሐፍ የተማርኩትን ይዤ ነው። ብላታ የአማርኛውን ሰዋስው ሲጽፉ መርሕ ያደረጉት የግዕዙንና የእንግሊዙን ሰዋስው ስለነበረ፥ “noun, pronoun, adjective, gender, singular, plural, etc.” ለሚባሉ ቃላት፥ “ስም፥ ተውላጠ ስም፥ ቅጽል፥ ጾታ፥ ነጠላ፥ ብዙ፥ ወዘተ” የተባሉትን የግዕዝና የአማርኛ ቃላት ሲመርጡላቸው፥ gender የሚለውን በ” ጾታ” ተረጐሙት። ዛሬ “ጾታ” የሚለው ቃል በተነሣ ቊጥር በብላታ ሰዋስው ባደገው ትውልድ አእምሮ ውስጥ የሚመጣው gender ነው። ብላታ “ጾታ” ን “gender” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል መተርጐሚያ አደረጉት እንጂ አልፈጠሩትም፤ የኖረ የግዕዝ ቃል ነው። ግን ግዕዝ የሚጠቀምበት በተለየ ለgender ብቻ ሳይሆን፥ በአማርኛ “ዓይነት” ፥ “ክፍል” ለምንለው ለማንኛውም ልዩነትን ለሚያሳይ ምልክት ሁሉ ነው። ለምሳሌ፥ የግዕዝ ሊቃውንት፥የተለያዩ የዜማ ዓይነቶችን “ጸዋትወ ዜማ” (የዜማ ዓይነቶች ወይም ጾታዎች) ይሏቸዋል። (“ጸዋትው” የ “ጾታ” ብዙ ቊጥር ነው ብያለሁ።) ብላታ መርስዔ ሐዘን genderን በጾታ የተረጐሙት የሰውን ዓይነት (ወንድ ይሁን ወይም ሴት) ሲያመለክት ስላዩት ነው። 

“ጾታ” የgenderንና የዜማን ዓይነቶች ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ብዙ ጸዋትው አሉ። እዚህ ጾታን የምጠቀምበት ሰዎችን በተፈጥሮና በባህል የተለያዩ ዓይነቶች የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማመልከቻ ነው። እነዚህ ነገሮች (ወይም ጾታዎች) የሰውየው የግሉ ናቸው። ለምሳሌ፥ አንድ ሰው ጾታው ወንድ ወይም ሴት (ወይም ፍናፍንት) ሊሆን ይችላል። ወንድነቱ ወይም ሴትነቱ (ወይም ፍናፍንትነቱ) የግሉ ነው፤ ይከበርለታል። ከፖለቲካ ውስጥ የመግቢያ ወይም እንዳይገባ የማገጃ መታወቂያ ሊሆን አይችልም። መታወቂያ ሊሆን የሚችለው የሴቶች ወይም የወንዶች ጉዳይ በሚታይበት ጊዜ ብቻ ነው። (የሴቶች ትምህርት ቤት አለ፤ የማዋለጃ ሐኪም ቤት አለ።) ሀገርና መንግሥት ግን የጋራ ስለሆኑ፥ በሀገር ፖለቲካ ወንዱም ሴቱም (ፍናፍንቱም) እኩል ይገባሉ፤ በሕግ ፊትም እኩል ይታያሉ።

አንድን ሰው “ይህ የግልህ ነው” የሚያስብሉት ብዙ ጸዋትው አሉ። ንግድ፤ ነጋዴዎች አንድ ጾታ ናቸው። ግብርና፤ ገበሬዎች አንድ ሌላ ጾታ ናቸው፤ ነገዶች/ጎሳዎች፥ ሐኪሞች፥
አስተማሪዎች . . . የተለያዩ ጸዋትው ናቸው፤ አባ ባሕርይ የዘመናቸውን የክርስቲያኑን ኅብረተ ሰብ ሲያጠኑ በጾታ ዘርዝረዋቸዋል። የጸዋትው አባላት ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ከፈለጉ መብት የሚሰጣቸው ማንነታቸው እንጂ ጾታቸው የሚገልጸው ምንነታቸው አይደለም። በዚያው አስተሳሰብ፥ ጾታቸው የሚገልጸው ምንነታቸው እፖለቲካ ውስጥ ከመግባት አያግዳቸውም። የሀገርም ሆነ የዓለም ፖለቲካ የሁሉም እኩል መብት ነው።

ዋና ዋና ታናናሽ የግል ጸዋትው፤

ከጸዋትው ሁሉ አንዱና እንደዋና የሚታየው ንኡስ ጾታ ሃይማኖት ነው። አፄ ኃይለ ሥላሴ፥ “አገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት የግል ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር (ወይም ዓዋጅ) ከአስሰሙበት ቀን ጀምሮ፥ ሃይማኖተኛውን ሕዝብ በሕግ ፊት በአንድ በኩል ግለኛ፥ በሌላ በኩል እኩለኛ ስላደረገ፥ ስፍር ቍጥር የሌለው ጊዜ ተጠቅሷል። መልእክቱ መንታ ነው፤ “እንደ ሃይማኖት ያለ የግል የሆነ ነገር የጋራ በሆነ ነገር (በመንግሥት ሥራ) ውስጥ አይግባ፤ የጋራ የሆነ ነገርም (መንግሥትም) የግል በሆነ ነገር ውስጥ አይግባ” የሚል ነው። ግን በዘመኑ ሥልጣኔ በተራመዱ አገሮች ውስጥ ሳይቀር፥ ብዙ የግል የሆኑ ነገሮች የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ እየገቡ ያስቸግራሉ። በዚያው አንጻር፥ መንግሥትና አንዳንድ ሰዎችም የግል በሆነ ጉዳይ ውስጥ እየገቡ ያስቸግራሉ። ዲሞክራት ሆኖ የዲሞክራሲን ሕግ መጣስ ነው።

የሀገር ጉዳይ የጋራ፥ የጾታ ጉዳይ የግል ሆነው መለያየት ያለባቸው ለምክንያት ነው፤ በአንድ በኩል ሕዝቡ ሀገሩ በምትሰጠው ጥቅም በሰላም እንዳይጠቀም መንግሥት በጾታው ምክንያት በግል ሕይወቱ ጣልቃ እየገባ እንዳያስቸግረው፥ በሌላ በኩል መንግሥት ሁሉንም እኩል ላገልግል ሲል፥ ሰዉ በጾታው ጣልቃ እየገባ ለጾታዬ ካላደላህ እያለ መንግሥትን እንዳያውክ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጾታን የግል የማድረግን ቁም ነገር በሕገ መንግሥት አጽድቆ፥ ሲሆን በውድ አለዚያም በግድ እግዚአብሔርን የሚፈራውንና የሚያከብረውን ያህል እንዲፈራውና እንዲያከብረው ካልተገደደ፥ በዘመኑ ሥልጣኔ የተራመዱ ሕዝቦች ከደረሱበት የብልጽግና፥ የዕውቀት፥ የጤንነትና የሰላም ደረጃ ልንደርስ አንችልም።

ይኸንን ስናገር ጠቢቡ ነቢይ፥ “እሳትና ውኻ አቅርቤልሃለሁ፤ እጅህን ከፈለከው ላይ አሳርፈው” ያለውን እያስታወስኩ ነው፤ ውኻ ቁሻሻን ያጸዳል፥ እሳት ያቃጥላል። ብዙ ሰዎች “ የምዕራባውያን ሕይወት እስከዚህም አያጓጓ” ይላሉ። እውነታቸው ሊሆን ይችላል፤ ለመበልጸግ የሚደረገው መሯሯጥ የመደሰቻ ጊዜ አይሰጥም። ግን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው ዓይነት፥ ኢትዮጵያዊ ገበሬ፥ ኢትዮጵያዊ አገልጋይ፥ ኢትዮጵያዊ ጫማ ጠራጊ ባለመኪና ቢሆን የሚጠላ ያለ አይመስለኝም። 

ወደ እምመኘው ዓዋጅ ልመለስና፥ ሊጸድቅ የሚገባው ሕግ፥ “ሀገር የጋራ ነው፤ ጾታ ግን የግል ነው” የሚል አጠቃላይ ሕግ መሆን አለበት። መቸም ሕገ መንግሥት ሲጻፍ የግል የሚባሉ ጸዋትውን ሁሉ መዘርዘር አይቻልም፤ ብዙዎች ናቸው። ግን ሕጉ በሚጸድቅበት ጊዜ ለምሳሌ ያህል ዋና ዋናዎቹን ብቻ አንሥቶ ማለፍ ይበቃል። ሌሎቹን በአንዳቸው ምክንያት ጭቅጭቅ በተነሣ ቍጥር ነፃውና ምሁሩ ዳኛ፥ “ይህ የጾታ ጉዳይ ነው/አይደለም” እያለ ሊፈርድ ይችላል። ሆኖም፥ ሃይማኖት መነሣት ካለባቸው የግል ጸዋትው አንዱና ቀንደኛው ነው። እርግጥ፥ ሃይማኖት የግል፥ መንግሥት የጋራ መሆናቸውን ሁላችንም ተቀብለነዋል፤ የቀረን በሥራ ላይ ማዋል እንጂ፥ ካሁን በኋላስ የሚያወያይ ጉዳይ አይደለም። ሌሎቹ የግል መሆን የሚገባቸው አለዚያ በባህል ጦርነት የሚያኖሩን ጸዋትወ ልሳን ናቸው። ቋንቋዎች ማለቴ ነው፤ ዝቅ ብዬ አብራራለሁ።

የባህል ጦርነት፤

የፖለቲካ ችግራችንን በጥሞና ብንመረምረው፥ ዛሬም ሆነ በታሪክ የሚያበጣብጠን በሃይማኖትና በቋንቋ የሚገለጸው ባህል ሆኖ እናገኘዋለን። የኢኮኖሚው ብጥብጥ ትናንት የመጣ ነው። ባህልንና ጠባዩን እንወቅ፤ ሰው ባህልን ይፈጥራል፤ ባህል ጸዋትውን ይፈጥራል። ጎሳዎች ሁሉ በአንድ በኩል የባህል አባቶች፥ በሌላ በኩል የባህል ልጆች ናቸው። ሕዝብን ለመከፋፈ የሃይማኖትንና የቋንቋን ያህል ኀይል ባይኖራቸውም፥ ያንድን ሀገር ሕዝብ የተለያዩ ታናናሽ ጸዋትው የሚያደርጉ ሌሎች ብዙ ንኡሳን ባህሎች አሉን። እነሱን ሁሉ፥ አንጋፋዎቻቸውን ሃይማኖትንና ቋንቋን ጨምረን የግል አድርገን እንደግል ካላየናቸው፥ የጦርነት ምክንያት ሆነውን ለበላይነት (የኔ ሃይማኖት፥ የኔ ቋንቋ፥ የኔ . . . ፣ የኔ . . . ፥ ይብለጥ እያልን) ስንፋጅ እንኖራለን። መፍትሔው ባለ ባህሎቹ የግል ባህላቸውን የግል አድርገው እንዲይዙ፥መንግሥትም ባህሎችን ለባለ ባህሎቹ እንዲተው በሕግ ማስገደድ ነው። ባህሎች ሕዝብን የሚጎዱ ወይም የሚያስገድዱ ካልሆኑ፥ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመከልከል ወይም በየትኛውም አቅጣጫ የመምራት ወይም መሪ የመሾም መብት የለውም። ግን አንዳንዶቹ ግለሰብንም ስለሚጎዱ (ለምሳሌ፥ የሴቶች ግዝረት፥ ከንፈር ላይ የሸክላ ሳህን መትከል . . .) እንዲቀሩ መንግሥት የማስተማር ግዴታ አለበት፤ ማስተማር ጣልቃ-ገብነት አይሆንም።

ባለባህሎቹ ቋንቋቸውን፥ ሃይማኖታቸውን፥ ዘፈናቸውን፥ እስክስታቸውን ለማዳበር ከፈለጉ፥ ሊያዳብሯቸው ሙሉ መብት አላቸው። ግን ከአባላቱ ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ያንን ባህል ማክበር ካልፈለጉ፥ (ለምሳሌ፥ የእስላም ሴቶች ፊታቸውን መሸፈን ካልፈለጉ) ወይም አንዱን ባህል ቢተዉት ወይም ትተው ወደሌላው ባህል ቢዛወሩ (ለምሳሌ፥ ሃይማኖታቸውንና ጎሳቸውን ቢለውጡ፥) ወይም ለመንፈሳዊ መሪነት ማንንም ቢመርጡ፥ ማንም ሊከለክላቸው መብት የለውም፤ ጾታ የግል ነው።

ያንኑ ያህል፥ አንዱ ጾታ በሌላው ጾታ (ለምሳሌ ክርስቲያኖች በእስላሞች ጉዳይ፥ እስላሞችም በክርስቲያኖች ጉዳይ) ውስጥ እየገቡ እንዳያስቸግሩ በጥብቅ መከልከል አለበት። ተናካሽ ውሻችንን፥ ተዋጊ በሬያችንን እንያዝ። ይኸንን እንደ ሃይማኖት አጥብቀን ካልያዝን፥ ትግላችን ለዶሞክራሲ ነው የምንለው በከንቱ ነው። ትግላችን ለግል ጾታችን (ለጎሳችን፥ ለሃይማኖታችን . . .) ብቻ ከሆነ፥ ድኽነት እንጂ ድኅነት አይኖረንም። “ብላ ባለኝ እንዳባቴ በቆመጠኝ” የሚባልባት ሀገር ይዘን እንቀራለን።

ጸዋትወ ልሳን (ቋንቋዎች)፤

ቋንቋና ሃይማኖት ሕዝብን የሚከፋፍሉና የሚያጋድሉ ጸዋትወ ባህል ናቸው ብለናል። ሃይማኖት የግል ሆኖ ሳለ፥ ሰዎች በጋራ ማምለክ መብታቸው ከሆነ፥ ቋንቋንም የጋራ መግባቢያ ማድረግ የማይደፈር ሰብአዊ መብት ነው፤ ይኼ አያከራክርም። ሆኖም ብሔራዊውን ቋንቋ በሁሉም ዘንድ እንዳይታወቅ የሚያሰናክል መስሎ ስለታየ፥ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ እንዳይሆኑ የተከለከሉበት ዘመን ነበር፤ አሁን ቀርቷል። 

ቋንቋ ሁለት የተያያዙ ጠባዮች አሉት፤ አንደኛ፥ ቋንቋ የአንድን ሀገር ሕዝብ በአንድ በኩል ብዙ ታናናሽ ጸዋትው (ኦሮሞ፥ ጉራጌ፥ ሱማሌ፥ አደሬ፥ ትግሬ፥ . . .) በሌላ በኩል አንድ ዓቢይ ጾታ (ጀርመናዊ፥ ፈረንሳዊ፥ ግብጻዊ፥ . . .) ያደርጋል። አንድን ሕዝብ ታናናሽ ጸዋትው የሚያደርጉ ቋንቋዎች ተናጋሪያቸው ሳያውቅ በአእምሮውና በአንደበቱ ውስጥ የሚበቅሉ ናቸው። ተናጋሪው ሲያድግ በሕፃኑ አእምሮና አንደበት ውስጥ አብረው ያድጋሉ። ሰውየውም ከዚህ ከአብሮ-አደጉና ከታማኝ አገልጋዩ ጋራ ፍቅር ይወድቃል፤ ከቀየው ጋር ፍቅር እንደሚወድቅ ማለት ነው። የማንነቱ መታወቂያው ይሆንና ያደላለታል። የልጁ አሳዳጊና ቋንቋ አውራሿ እናቱ ስለሆነች፥ ይህ ቋንቋ “የእናት ቋንቋ” ወይም (የልጁ መጀመሪያ ቋንቋው ስለሆነ) “አፍ መፍቻ ቋንቋ” በመባል ይታወቃል። “በእናት ቋንቋ” (“በአፍ መፍቻ ቋንቋ” ) ምክንያት የአንድ ሀገር ሕዝብ ብዙ “ጸዋትወ ነገድ” ይወጣዋል። የነገድና የጎሳ መነሻ (ጥንተ መሠረቱ) ዘር ሊሆን ይችላል፤ እየመሰለንም የዘራችን መታወቂያ ላደረግነው ቋንቋ ጥብቅና እንቆማለን። መታወቂያችን መሆኑ እርግጥ ነው፤ የዘራችን መታወቂያ መሆኑ ግን ቀርቷል። ዘር ስለተደበላለቀ፥ ዛሬ ያ ቀርቶ፥ የጎሳ መሠረቱ ቋንቋ ሆኗል። ቋንቋ እየገፋ፥ ንጹሕ ዘር እየጠፋ ሄዷል። እነዚህ ቋንቋዎች የዘር ቋንቋ ያልተባሉት፥ ቢባሉም ስሕተት የሚሆነው ስለዚህ ነው። “ቋንቋዬ ዘሬን ይነግረኛል” የሚል ሰው ካለ፥ ሊሳሳት እንደሚችል ልብ ይበለው። “አማራ ነኝ፤ ኦሮሞ ነኝ፤ ጉራጌ ነኝ፤ . . .” የምንለው ማንነታችንን ባህላችን ወስኖልን ነው።

ሁለተኛ፥ “የእናት ቋንቋ” (“አፍ መፍቻ ቋንቋ” ) ብዙ ጸዋትው ያደረገውን የአንድን ሀገር ሕዝብ አንድ ቋንቋ ነግሦ፥ አንድ ዓቢይ ጾታ ያደርገዋል። ለምሳሌ፥ “የእናት ቋንቋዎች” (“አፍ መፍቻ ቋንቋዎች”) እነ ስፓንኛ፥ ጣሊያንኛ፥ ፈረንሳይኛ፥ ጀርመንኛ፥ ዓረብኛ፥ ኦሮምኛ . . . ብዙ ታናናሽ ጸዋትው ያደረጉትን የአሜሪካንን ሕዝብ እንግሊዝኛ አንድ ዓቢይ ጾታ አድርጓቸዋል፤ አንድ የአሜሪካ ሕዝብ አድርጓቸዋል። እንግሊዝኛ የአሜሪካ ሕዝብ የጋራ መታወቂያ ሆኗል።

አንድ መንግሥት አንድ ቋንቋ፤

በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ሕዝብ አንድ ቤተሰብ የሚሆነው አንድ ዓቢይ ጾታ የሚያደርገው ነገር (የጋራ መታወቂያ) ሲኖረው ነው። ያ ነገር ብዙ ጊዜ ቋንቋ ነው። አንድ ሕዝብ ለመሆን፥ ሁሉ የሚያውቀውና የሚገናኝበት አንድ ሀገር-አቀፍ ቋንቋ ቢኖረው ይመረጣል። ሌሎች መታወቂያዎች ሕዝብን አንድ ለማድረግ የቋንቋን ያህል ኀይል የላቸውም። ግን ሕዝቡ አንድ ሕዝብ ለመሆን የሚግባባበት ቋንቋ አንድ ብቻ መሆን አለበት ወይ? ቋንቋ የሚያስፈልገው ለመግባቢያ ብቻ ከሆነ፥ አንድ ይበቃል፤ የክትና የአዘቦት ቋንቋ አያስፈልገውም። ጾታዎች ከፈለጉ በጾታ ደረጃ በየራሳቸው ቋንቋ እየተናገሩ፥ በሀገር ደረጃ ሁሉም በሚገናኝበት መገናኘት ይችላሉ። ለአንድ አገር አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ማስፈለጉ አያጠያይቅም። ለምሳሌ፥ “የእናት ቋንቋዎች” የህንድን ሕዝብ ከአንድ ሺ ጸዋትው በላይ ከፋፍለውታል። እነዚህን ቋንቋዎች የግል መጠቀሚያ ከማድረግ አልፎ ሁሉንም በሀገር-አቀፍ ደረጃ መጠቀሚያ ማድረግ አይታሰብም። ታዲታ ምን ይሻላል?

ለሀገር ከታሰበ፥ ለሀገር የሚሻለው ከብዙዎቹ ቋንቋዎች ውስጥ የትኛው ቋንቋ ይመረጥ ከሚለው ላይ በጥሞናና በኀላፊነት ማትኰሩ ነው። ከብሔራዊ ቋንቋ ምርጫ ላይ የሚደረሰው በሁለት መንገድ ነው፤ አንደኛው መንገድ ታሪክ የተጓዘበት ሂደት ነው። ታሪክን ስንመረምር፥ ከመጀመሪያው ላይ፥ የየጎሳቸውን ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ሰዎች ሲገናኙ በንግግር ለመግባባት ብዙ ይጥራሉ። ዋናው መገናኛቸው ቦታ ገበያ ነበር። ገንዘብ በሌለበት ዘመን ሲገበያዩ ሸቀጥ በሸቀጥ እየተለዋወጡ ነበር። የሸቀጦቹን ስም ሸቀጦቹን ባመጣቸው ሰው ቋንቋ (በነጋዴው ቋንቋ) ለማወቅ ይኸ አጋጣሚ ጥሩ ዕድል ይሰጣል። ነጋዴው ሸቀጡን በራሱ ቋንቋ እየጠራ እንዲገዙት ያስሰማል--” ጨው! ጨው! ዶቃ! ዶቃ! . . .! ይላል።

ሌላው አጋጣሚ የመንግሥት ሥልጣንና የሃይማኖት መስፋፋት ናቸው። ሥልጣኑንና የሃይማኖቱን ዕውቀት የሚያደርሱ ሰዎች አዲስ ነገር አቅራቢዎች በመሆናቸው ሚናቸው የመከበርና የመሰማት ዕድል ይሰጣቸዋል። ቋንቋቸውን ማወቅ ያጓጓል፤ እርምጃም ይወሰድበታል። አቤት እንግሊዝኛ ለማወቅ የነበረን ጒጒት!!

አንድን ቋንቋ በሂደት በብዙ ቦታ እንዲታወቅ የሚያደርገው ሦስተኛው ምክንያት የተናጋሪው ሕዝብ ብዛት ነው። ለምሳሌ፥ በአማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የተከበቡ ቅማንቶች፥ ወይጦዎች፥ ሺናሻዎች፥ ፈላሻዎች፥ ኳኵራዎች፥ ጋግራዎች አማርኛ ሲናገሩ ቢታዩ አያስገርምም። ኦሮሞዎች ከደቡብ ወደሰሜን ሲፈልሱ ያጥለቀለቋቸው ጎሳዎች ኦሮምኛ ተናጋሪዎች፥ መጤዎቹ ኦሮሞዎችም የነባሮቹን ቋንቋ ተናጋሪዎች ሆነዋል። ይኸ ሁሉ ዐውቆ የመጣ የታሪክ ሂደት ነው።

ሁለተኛው መንገድ ሰው-ሠራሽ ሂደት ነው። አንድ ሕዝብ የራሱን መንግሥት ለማቋቋም ሲፈልግና ሲስማማ፥ ከሁሉ አስቀድሞ (1) ማንነቱን፥ (2) የቆመበትን ምድር ዳር ድምበር፥ (3) የሚገናኝበትን ቋንቋ፥ (4) ማንነቱን የሚገልጽበትን ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር (National Anthem) ይወስናል። በዚህ መንገድ የሚሄዱ ወጣት አገሮች፥ በተለየም ቅኝ ገዢዎች የፈጠሯቸው (ለምሳሌ፥ እንደ ኢንዶኔዢያ ያሉ) አገሮች ነፃ ሲወጡ የሚሄዱበት መንገድ ነው። ግን ሰዎች ለቋንቋ የበላይነት ክብር ስለሚሰጡ፥ በምርጫ ጊዜ ጥቅሙን ከማየት ይልቅ ሁሉም “ማን ከማን ያንሳል? እኔ የምናገረው ቋንቋ ይመረጥ” የሚል ዐድላዊነት ይደነቀርና በጽሞናና በገለልተኝነት መመለስ ያስቸግራል። “ከራስ በላይ ሀገር” የሚለው ሀገር ወዳድነት ሁሉ ይቀርና “ከራስ ቋንቋ በላይ ነፋስ” የሚል መንፈስ ይሰፍናል። ዓለም በተቀራረበበት በአሁኑ ዘመን እንዲህ ማሰብ ደንቃራና ኋላ-ቀር መሆን ነው። ብዙ አፍሪካውያን ዳር ድምበራቸውን ወስነው ሀገር በፈጠሩላቸውና ስም በአወጡላቸው በቅኝ ገዢዎቻቸው ቋንቋ ጸንተዋል።

በኢትዮጵያስ? ኢትዮጵያማ አሮጊት አገር ናት፤ ቊጥሯ ከወጣቶቹ ጋር አይደለም። ራስ-ፈጠር ናት፤ ቊጥሯ ከጥንት አገሮች እንጂ ከአውሮፓ-ፈጠር አገሮች ጋር አይደለም። ሊቃውንቱ ታሪኩን ከምናውቀው የአክሱም ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ፥ ብራና እየፋቁ ይጽፉ ነበረ። ለጥንቱ ማስረጃ የሚፈልግ የሎሬል ፊሊፕሰንን ጥናት ማንበብ ይችላል (Laurel Phillipson, “Parchment Production in the First Millennium BC at Seglamen, Northern Ethiopia,” published online: 15 August 2013). ከጥንቱ ወዲህም፥ መጀመሪያ፥ በግዕዝ፥ በግሪክ፥ በሳብኛ፥ በኋላ በግዕዝና በአማርኛ ደብተራዎቹ የመዘገቧቸው ሰነዶች በየቤተ መጻሕፍቱ ይገኛሉ። በሐረርና በወሎ የእስላም ዑለማእ (“ዑለማእ” የዓሊም ብዙ ቊጥር ነው “ደብተራዎች” እንደ ማለት ነው) በዐረቢ ፊደል የጻፏቸው የአማርኛ ሰነዶች ተገኝተዋል። ባጭሩ፥ ኢትዮጵያ መገናኛ፥ በኋላም መተዳደሪያ ቋንቋዋን የታሪክ ሂደት ወስኖላታል። ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ያ ቋንቋ አማርኛ ነው።

ግን “ቋንቋዋን ታሪክ ወስኖላታል” ማለት የተያያዘ ችግር የለባትም ማለት አይደለም። ታሪክ ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላ የመጡ ጎሳዎች (ኦሮሞዎች) እና ጥንታውያን ነን የሚሉ ቋንቋቸው ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መጻፊያ ያልነበረ ጎሳዎች (ትግሬዎች) ውሳኔውን መቀበል አልፈለጉም፤ እንሱንና ቋንቋቸውን የሚያዋርድ መሰላቸው። ለምሳሌ፥ የተማሪዎቹ ንቅናቄ “የጎሳዎች መብት ይከበር” ይል የነበረው፥ ደርግ ሸንጎውን ሲከፍት፥ የተማሪዎቹን ጩኸት በማስተጋባት፥ “በምን ቋንቋ እንነጋገር” የሚል ጥያቄ አቅርቦ የነበረው፥ የችግር መኖር ምልክት ነው። አማርኛን የአማሮች ቋንቋ አድርገው፥ “ቋንቋቸውን” ብሔራዊ ቋንቋ በማድረግ ከቀጠልን፥ ለአማሮች የበላይነት መስጠት ይሆናል ብለው ነው። በዚህ ምክንያት፥ ቋንቋን የአንድነት ምልክት ማድረግን ታላቅ ክብር ተነግፈናል፤ ሌላም አደጋ አለው። ሁሉም የአማርኛንና የአማሮችን ታሪክ አለማወቅ ያመጣው ብሔራዊ ችግር ነው።

ከአማሮቹ አብዛኛዎቹ አማራ የሚባሉት የጎሳ ቋንቋቸውን ትተው አፋቸውን የፈቱት አብዛኛው ሕዝብ በሚናገረው በአማርኛ ስለሆነ እንጂ በዘር ንጹሕ አማራ በመሆናቸው አይደለም። ምን ማለቴ እንደሆነና አማሮች እነማን እንደሆኑ፥ ባጭሩም ቢሆን፥ እታች “አዲስ አማሮች” በሚለው ንኡስ ክፍል ላስረዳ እሞክራለሁ።

ክልል በቋንቋ፤

ሆኖም፥ አገሪቱ የሕዝብ ስለሆነች ሕዝብ በነፃ ምርጫ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፤ ጥያቄው ከሕዝብ ከመጣና ምርጫው በነፃ የሚፈጸም ከሆነ፥ በዲሞክራሲ የሚያምን ሰው የሕዝብን ውሳኔ ማክበር ግዴታው ነው። እንደምገምተው፥ የሕዝቡ ፍላጎት፥ ዲሞክራሲን ዳኛ አድርጎ በነፃነት፥ በእኩልነት፥ በጤና፥ በጥጋብ በተንጣለለ መሬት ላይ ወደ ፊት መጋለብ ነው። ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ አንድነታችንን የሚያሰጉትንና የተንጣለለ መሬት ሊነፍጉን የሚችሉትን የግል ታናናሽ ጸዋትው፥ በሀገራዊ አስተዳደር እንዳይገቡ በጥብቅ መከልከል ይሆናል። ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ፥ ለባህል ጦርነት የዳረጉን ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች ናቸው ብለናል።

ወያኔዎች ሕዝባችንን በቋንቋ የከፋፈሉት በሀገራችን የተጫረውን የባህል ጦርነት ለማቆም ከሆነ፥ ውጤቱ በተንጣለለው የሀገራችን መሬት ላይ በፍቅር-አልባ ጉርብትና የሚኖሩ ታናናሽ ሀገሮች መፍጠር ነው። ባልና ሚስት ሲጣሉ ማፋታት ትዳራቸውን ማፍረስ ነው። አፋትቶ፥ “አብራችሁ ኑሩ” ማለት ሞኝነት ወይም ሌሎችን ማሞኘት ነው። አንድ ሀገር ብዙ ሀገሮች እንዲሆን ከተፈለገ፥ ከዚህ የተለየ አይደረግም። አንድ ሕዝብ በሃይማኖትና በቋንቋ ከተከፋፈለና ሁሉም የቆሙበት ቀየ እየተከለለ ከታደለው፥ ለአንድነት መቃብር መማስ ነው። ኢኮኖሚ ብቻውን አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ አያደርግም። እንዲያውም፥ አለክልሉ የተገኘ ሌላ ሃይማኖት ያለውና በሌላ ቋንቋ የሚናገር ዜጋ እየታደነ ከቀየው ይባረራል (ዘር ማጽዳት ይከተላል) ወይም እንደ ባይተዋር በጥብቅ ክትትል ይስተናገዳል። ይህ ከሆነ፥ የሀገር አንድነት በስም እንጂ፥ እውነትነት አይኖረውም። በላያቸው የፌደራል መንግሥት ማቋቋምና ፕሬዚዴንት መሾም የሀገርን አንድነት አይጠብቅም፤ ለተባበሩት መንግሥታት (UN) ዋና ጸሐፊ ከመሾም አይለይም። “ልገንጠል ካለ፥ በጦር እናስገድደዋለን” ማለት ከሆነም፥ በግድ ሰድዶ በግድ ማሳደድ ይሆናል።

ባሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ገዢዎች ሀገሪቱን ለምን እዚህ ዳክራ ልትወጣው ከማትችልበት ማጥ ውስጥ እንዳስገቧት በእርግጠኝነት የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። የሰማሁትና ያመንኩትም፥ “የአማራውን ገዢነትና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን የበላይነት ለማስቀረት ነው” ሲባል ነው፤ ግን አይመስለኝም። ፍርሃታቸው ይህ ቢሆንማ ፍቱኑ መፍትሔ፥ “አንድ ድምፅ ለአንድ ሰው” የሚፈቅደውንና ሕዝብ የተዋደቀለትን ዲሞክራሲን ማወጅ ነበር። ይኸንን ቢያውጁ፥ ሕዝቡ ለአስተዳዳሪነት የሚመርጠው ይጠቅመኛል የሚለውን እንጂ፥ የዚህ ጎሳ ሰው ነው ወይም ሃይማኖቱ እንዲህ ያለ ነው የሚለውን አይሆንም።

እንደ እውነቱ ከሆነ፥ የሚፈልጉት ሲገዙ ለመኖርና ሲዘርፉ የሚናገራቸውን፥ ማንንም ሳይፈሩ እንደፈለጉ እንዲገድሉ ነው። አለዚያማ፥ እድሜ ለአማራ ልጆች፥ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የበላይነት አብዮቱ የተጀመረ ጊዜ በአስከፊ ሁኔታ ቆሟል። “አስከፊ ሁኔታ” ያልኩት አብዮተኞች ነን የሚሉ ርእሰ ብሔሩን የመርዝ ጪስ አሸትተው፥ በትራስ አፍነው፥ ርእሰ ኦርቶዶክሱን በሽቦ አንቀው መግደላቸውን በማስታወስ ነው። ካልገዛን አገር ትውደም ከሚል ውሳኔ የደረሱና ታጥቀው የተነሡ፥ የትግራይም ሆነ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጎሳ የማይደግፋቸው ዱርየዎች ናቸው።

የአማራ ገዢነት፤

የአማራ ገዢነት የሚባለውም በገለልተኝነት መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው። መንሥኤው የኢትዮጵያ መንግሥት የአማሮችን ቋንቋ (አማርኛን) በመናገሩ ነው። የአሜሪካን መንግሥት ቋንቋ እንግሊዝኛ ስለሆነ፥ ገዢዎቹ እንግሊዞች ናቸው እንደማለት ነው። እርግጥ እንግሊዞች አንድ ጊዜ አሜሪካንን ገዝተው ነበር። አሁን የሉም፤ ያለው ድብልቅልቁ የአሜሪካ ሕዝብ የወረሰው ቋንቋቸው ነው።

የአማርኛና የአማሮች ሁኔታም በከፊልም ቢሆን ተመሳሳይነት አለው። አንድ አማርኛ ከሚናገር ቤተ ሰብ የወጣ ይኩኖ አምላክ የሚባል ጀግና በ1262 ዓ. ም. የኢትዮዮጵያን መንግሥት ከዛጔዎች ወስዶ ዛጔዎች ከመንኮታኰት ያላዳኗትን ሀገር እንደገና አቋቁሟት እንደነበረ ይታወሳል። ይኩኖ አምላክና ቤተ መንግሥቱ አማርኛ ስለተናገሩ፥ “አማርኛ የሀገሪቱ ዋና መገናኛ ሆነ” የሚሉ አሉ፤ ስሕተት ነው። ይኩኖ አምላክ ኢትዮጵያን ከመጀመሪያው ዘመነ መሳፍንት ማውጣቱ፥ እሱና ልጆቹ ሀገሪቷን በዓለም ደረጃ እንድትታፈር ማድረጋቸው፥ አማራ ነኝ የሚለውን ሁሉ የሚያኮራና ትምክሕተኛ የሚያደርግ እውነታ ነው፤ ለዚህም አገር-ወዳድ ሁሉ ያመሰግነዋል።

አማርኛ ግን ይኩኖ አምላክ ከመነሣቱ ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መነጋገሪያ ነበር። “በዘር ንጹሕ አማራ ነኝ” የማይለው ይኩኖ አምላክም አማርኛን የራሱና የቤተ መንግሥቱ ቋንቋ ያደረገው ሁኔታ አስገድዶት ነው። ምክንያቱም፥ መንግሥት ያቋቋመው የመገናኛ ዓቢይ ቋንቋው አማርኛ በሆነው ሕዝብ ላይ ነበር። ስለዚህ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የቤተ መንግሥቱን ቋንቋ ወሰደ ከማለት፥ ትክክሉ ቤተ መንግሥቱ በሕዝብ ቋንቋ ተጠቀመ ማለቱ ነው። ኢማም አሕመድ (ግራኝ) በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ወታደሮቹን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሲያዘምት በአማርኛ ብቻ እንዲነጋገሩ የመከራቸው ለዘዴው ቢሆንም፥ በዚያ ዘመን አማርኛ ዛሬ የአፍሪካ ቀንድ በሚባለው ክፍለ አፍሪካ የመገናኛ ቋንቋ እንደነበረ ያስረዳል። የተምቤኑ ተወላጅ አፄ ዮሐንስና ከእሳቸው በፊትና ከእሳቸው በኋላ የገዙ የትግራይ መኳንንት (እነሰባጋዲስ፥ እነ አሉላ) ግዛታቸውን ያካሄዱት በአማርኛ ቋንቋ እንደነበረ ትተዋቸው ያለፉት ሰነዶች ይመሰክራሉ። ማወቅ ለሚፈልግ አማርኛ እንዴት እንደተስፋፋና ከግዕዝ ጋር እየተጣላ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንደሆነ የሚያስደንቅ ታሪክ አለው። ገለልተኛ ሆኖ ለሚፈርድ ሰው፥ (አገር- ወዳድም ሆነ አገር-ጠላ) አማርኛን ከብሔራዊ ቋንቋነት ለማውረድ አጥጋቢ ምክንያት አያገኝም።

እስቲ እንዳይፈረድብን አድርገን እንፍረድ፤ አማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ የተቋቋመ መንግሥት አማርኛን ትቶ በምን ቋንቋ ይነጋገር? የኢትዮጵያ መንግሥት አማሮች ያቋቋሙት መንግሥት ነው ማለት እውነትነት አለው። አማሮች የሚኮሩትና ትምክሕት የሚሰማቸው በሚገባ ነው። አፍሪካውያን አባቶቻቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እየተረዳዱ እንደጥንት ሕዝቦች ብሔራዊ መንግሥት አቋቁመው፥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እየተረዳዱ የሀገሪቷን ሥነ ጽሑፍ አዳብረው፥ አልፎ አልፎ ለሌሎች አገሮችም ተርፈዋል። ታዲያ እነሱ በአባቶቻቸው ሥራ ያልኮሩ፥ ያልተመኩ ማን ይኩራ፥ ማንስ ይመካ? መቸም ቢሆን አባቶች ልጆቻቸውን የሚያኮሩት የሚያኮራ ታሪክ ሲፈጽሙ ነው። ያባቶቻችን ታሪካቸው ሲያነቡትና ሲያስነብቡት ያኮራል፥ ያስቀናል። አማሮችን መውቀስና አስተዋፅኦዋቸውን ከአውሮፓውያን አስተዋፅኦ አሳንሶ ማየት ራስን መናቅ ነው። የሚሻለውስ አማራ የብዙ ጎሳዎች ውጤትና መናኸሪያ መሆኑንና የሚያኮራው ታሪኩም የጎሳዎች ሁሉ (የሁላችንም) ታሪክ መሆኑን ተረድቶ አብሮ መኵራት ነው። አለዚያ፥ “ትኮራበት የላት ትንቀው አማራት” ይሆንብናል። የሚያኮራው ታሪካችን የጋራ እንደሆነ ማሳየት ካስፈለገ፥ ሳልሰለች ዛሬም እንደገና ላስረዳ እሞክራለሁ። ግን አንድ አባ ምናሴ የሚባሉ የነገረ መለኮት መምህር እንዳሉት፥ “በክሕደት የተቈራኘ ሰይጣን በደግዳጋ [በሰላም፥ በጤና] አይለቅም።”

ይኩኖ አምላክ ያቋቋመው መንግሥት ቋንቋው አማርኛ መሆኑ ለቋንቋው ለመስፋፋት ረድቶታል ብሎ መገመት ይቻላል። የተሻለው ግምት ግን፥ አማርኛ ለብሔራዊ መሰባሰብና መጠቃለል (National integration) መሠረት ሆኗል ማለቱ ነው። አማርኛ የሰፊው ሕዝብ ቋንቋ ከመሆኑ በተጨማሪ የመንግሥት ቋንቋ ስለሆነ፥ መነሻቸው አማራ ያልሆኑ ሰዎች ቋንቋቸው አድርገውታል። ከዚያም አልፈው የናት ቋንቋ/አፍ መፍቻ ቋንቋ አድርገውታል። በአማራነት በኩል የአንድ መንግሥት፥ የአንድ ሀገር ሕዝብ ሆኑ ማለት ነው። አዲስ ነገር አይደለም፤ ጥንታዊ አገር ሁሉ ብሔራዊ መሰባሰብና መጠቃለል (National integration) የፈጸመው በአንድ ቋንቋና በአንድ ኢኮኖሚ ላይ ነው። መሰባሰብ ካልቀረ፥ በሀገር ቋንቋ ብንሰባሰብ፥ ነውሩና ቁጭቱ ለምንድን ነው? ከሆነ በኋላ መጥቶ “ለምን በእኛ ቋንቋ አልተሰባሰብንም?” የምንል ከሆነ፥ ባቡሩ ጣቢያውን ከለቀቀ በኋላ መጥቶ፥ መራገምና ሁከት መፍጠር ነው። ሲታሰብ፥ አዲሶቹ አማሮች በቍጥር የጥንቶቹን አማሮች ሳይበልጧቸው አይቀርም። በዘር ከሄድን፥ የጥንቶቹ አማሮች አሁን ሁሉም የሉም፤ በሌሎች ተውጠዋል። ያለው የተወረሰው ቋንቋቸውና ስማቸው ነው። በመደበላለቅ ታሪካችን ምክንያት፥ ራሱ ቋንቋቸውና የቀረው ባህላቸውም ተለውጧል። እነሱ ሲዋጡ የተለወጠው ቋንቋቸውና ስማቸው የተረፈው፥ (1) መንግሥቱ በሰላም ወዲያ ወዲህ መጓዝና መነገድ የሚያስችል ጽኑ መንግሥት ስለነበረ፥ (2) የሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ትውፊት እየዳበረ ስለሄደ ነው። ተመሳሳይ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ፥ አግዓዝያን ዛሬ የሉም፤ ተውጠዋል፤ ቋንቋቸው ግን አለ። አግዓዝያን ሳይኖሩ ቋንቋቸው ግዕዝ የኖረው የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ስለሆነና የሀገሪቱ መንግሥት መሠረተ-ጽኑ ስለነበረ ነው።

አዲስ አማሮች፤

“አሁን የጥንቶቹ አማሮች የሉም” ስል፥ “አማሮች ነን” የሚሉት ከመቆጣታቸውና አጥቂዎቻቸው ከመሳለቃቸው በፊት እንዲህ ያልኩበትን ምክንያት እንደገና ላብራራ። እርግጥ፥ “አማራ ነን” የሚሉ ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፤ አንዱ እኔ ራሴ ነኝ። ግን እንዲህ ነው፤ አማሮች የሚኖሩበት አምሐራ የሚባል ክፍለ ሀገር ነበረ። ክፍለ ሀገሩም ሰዎቹም አምሐራ ይባሉ ነበር-- ጥንትም ዛሬም ክፍለ ሀገሩንም ሰዎቹንም “ትግሬ” እንደምንል ማለት ነው። ግን የዱሮ አማሮችና ዛሬ አማሮች ነን የሚሉት አንድ አይደሉም፤ በታሪክ ሂደት፥ የሌላ ጎሳ ሰዎችም አማሮች ስለሆኑ፥ ዛሬ አማራ ስንል በዘር መሆኑ ቀርቷል። ልብ በሉ፤ ሐርላ፥ ጋግራ፥ የሚባሉ ነገዶች ነበሩ። ዛሬ “ሐርላ ነኝ” ፥ “ጋግራ ነኝ” የሚል አንድም ሰው የለም፤ ጠፍተዋል ማለት ሳይሆን፥ ቋንቋቸው አማርኛ ምናልባትም ኦሮምኛ ሆኗል፤ አማርኛና ኦሮምኛ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር በጋብቻ ተደባልቀዋል፥ ቋንቋቸውንም ወርሰዋል ማለት ነው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፥ ጎንደር (ስሜን)፥ ጎጃም፥ ሸዋ የአምሐራ ክፍል አልነበሩም። ቋንቋው ግን በነዚህ ክፍለ ሀገሮች ነግሧል፤ ያነገሡትና የነገሠባቸው ሰዎቹም “አማራ ነን” ይላሉ።

እነሱን እንተዋቸው፤ ቋንቋቸው አማርኛ የሆነበት ዘመን እጅግ ሩቅ ስለሆነ፥ ዝርዝሩን መናገር ይጸንነናል። ወደቅርቡ ዘመን እንምጣና፥ ዛጔዎች ሲገዙ ቋንቋቸው አገውኛ ነበር። ዛሬ ልጆቻቸው (ዋግሹሞችና ሌሎቹም) ከማህላችን አሉ፤ ግን አንዳቸውም አገውኛ አያውቁም፤ አማርኛ ተናጋሪዎች ሆነዋል፤ አማራ ሆነዋል፤ በአማራነት ወደአንድ ጾታ ተጠቃልለዋል። “አማራ እየገፋ፥ አገው እየጠፋ ሄደ” የሚል አነጋገር የመጣው ስለዚህ ነው። መሆን የነበረበት “አማራነት እየገፋ፥ አገውነት እየጠፋ ሄዱ” ነበር። ሐርላዎችንና ዛጔዎችን የሚመስሉ ብዙ ነገዶች ነበሩ፤ ልጆቻቸው ሁሉም አማርኛ ተናጋሪዎች (አማሮች) ሆነዋል። ስንቱን እዚህ ልጥቀሰው ማለት ነው እንጂ፥ የጻድቃኖቻችንን ገድል ስናነብ የምናገኘው ይኸንን ነው። ለቅሞ ቢያሳትሙት አንድ መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል፤ ግን ጥቂቱን ያላመነ ብዙውን አያምንም። ኦሮሞዎች ወደማህል ኢትዮጵያ ከፈለሱበት ከዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት በኋላማ የተደባለቀው የአማራ ሕዝብ የባሰውን ተደበላልቋል። እነዚህ አዲስ አማሮች የአማራን ቋንቋና አባሪ ባህሎች ስለወረሱና ስላዳበሩት፥ “አማራ ነን” ይላሉ፤ ሊሉ የሚገባቸው ግን “አማርኛ ተናጋሪዎች ነን” ነበር።

ግድ የለም፤ ምሥጢሩ እስከታወቀ ድረስ ምንም ቢባሉ ጒዳት የለውም። ግራም ነፈሰ ቀኝ፥ እነዚህ ሰዎች የአማራ፥ የአገው፥ የሐርላ፥ የጋግራ፥ የአርጎባ፥ የሽናሻ፥ የቦሻ፥ የፈላሻ፥ የኦሮሞ፥ የወላይታ፥ የትግሬ፥ የጉራጌ፥ የብጌ፥ የጎንደሬ፥ የጋፋቴ፥ የጎጃሜ፥ . . . ድብልቆች ቢሆኑም፥ እንዳንድ ነገድ ታይተዋል። እነሱም አምነውበታል። ንኡስ ጾታ የሚያደርገውን የየናት ቋንቋቸውን ትተው ዓቢይ ጾታ የሚያደርገውን አማርኛን አፍ መፍቻቸው/የናት ቋንቋቸው አድርገውታል። ኀደግነ ኵሎ ወተለውናከ እንዳሉት፥ ሁሉንም ትተው፥ መንግሥቱን በመከተል ሀገር-አቀፍ ወይም መንግሥታዊ ነገድ ሆነዋል። ግን አስፈላጊነቱ አልታያቸውም፥ ሁኔታውም አልረዳቸውም እንጂ፥ ጥለውት የመጡትን ቋንቋም (አገውኛን፥ ሐርልኛን፥ ኦሮምኛን፥ ወላይትኛን፥ ጉራግኛን፥ ወዘተ.) በተጨማሪ ቢናገሩ ኖሮ፥ (ሌሎች አሁንም እንደሚያደርጉት ማለት ነው) ከዘመዶቻቸው ጋራ የነበረው ቀጥታ የባህል ዝምድናቸው አይቋረጥም ነበር። ስለተቋረጠ፥ ሃይማኖቱን እንደለወጠ ሰው ተራርቀዋል። መራራቅ ብቻ ሳይሆን፥ እንደ ተቀናቃኝ የሚያዩዋቸውና የጎሳ ፓርቲ አቋቁመው የባህል ጦርነት የገጠሟቸው ጥቂቶች አይደሉም። ኢኮኖሚውን መሠረት አድርገን ብሔራዊ ችግራችንን (ድኽነትን፥ ድንቁርናን፥ በሽታን፥ ጭቆናን፥ . . .) እንዳናስወግድበት ትልቁን ጦርነት ባህል ቀለበሰብን። እንዲያውም አንድነታችንን ከአደጋ ላይ ጣለው። የቅድመ አያቶቻቸውን ቋንቋ ትተው አፋቸውን የፈቱት ሰፊው ሕዝብ በሚያውቀውና የኢትዮጵያን መንግሥት ከወደቀበት ባነሡት ሰዎች ቋንቋ (በአማሮች) ስለ ሆነ፥ መንግሥቱን የጠላ ባለሌላ ቋንቋ ሁሉ አብሮ ያገልላቸው ጀመር--” ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወገጥ” እንዲሉ። ንጉሣዊው አገዛዝ የተጠላው ግን በአማርኛ ተናጋሪዎች ጭምር ነበር። ምክንያቱም መንግሥቱ ሕዝብን ሲጨቁን አማርኛ ተናጋሪውን ለይቶ አልማረም። ሰዎች በዘልማድ “የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች” ሲሉና አማርኛ ተናጋሪውን ከዝርዝራቸው ውስጥ ሳያስገቡ ሲቀሩ ይገርመኛል።

በአሁኑ ሰዓት አማርኛ ተናጋሪዎች (አማሮች) “ጨቋኞች” ይሏቸው የነበሩትን ያለፉ ገዢዎቻችንን ሲያከብሩ እናያቸዋለን። ይኼ ደግሞ ራሳቸውን ከገዢው ጋር ያሰለፉ ያደርጋቸውና በሌሎች ዘንድ የበለጠ ያስገልላቸዋል። በማህል ቤት ተጠቃሚው ወያኔ ነው። እንደ እውነት ከሆነ፥ አማርኛ ተናጋሪዎቹ ያለፉ ገዢዎችን የሚያከብሩት የአንድነት ታሪካችን መሪዎች ስለነበሩ እንጂ፥ ከገዢው ወገን ስለሆኑ አይደለም። ራሳቸውን ከገዢው ወገን ቢያደርጉ ኖሮማ፥ ንጉሣዊውን አገዛዝ ለመጣል ሲታገሉ ከማንም ይበልጥ እንደ ቅጠል አይረግፉም፥ መንግሥቱም አይወድቅም ነበር።

የአንድነትና የጋራ ታሪካችን፤

የኢትዮጵያ ታሪክ ከፋም ለማ ገዢዎቿ እየመሯቸው የሁላችንም አባቶች የሠሩት መሆኑን በአጋጠመኝ ቊጥር ሳላነሣውና ማስረጃ ለመስጠት ሳልሞክር ቀርቼ አላውቅም። ምናልባት ብናገረውም፥ ሳላጎላው የቀረሁት፥ ታሪኩን የፈጸሙት አማራ የሆኑት ጎሳዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ በጎሳቸው (በኦሮምነታቸው፥ በጉራጌነታቸው፥ . . .) ያሉ ሁሉ መሆኑን ነው።

አያቶቻችን ኢትዮጵያን የታሪክ ሀገር ሲያደርጓት ራእይ እየሰጡ የመሯቸው ነገሥታቱ ናቸው። ነገሥታቱ አጠፉም አለሙም ባለውለታችን ናቸው። ዔዛና፥ አብርሃ አጽብሐ፥ ካሌብ፥ ገብረ መስቀል፥ ላሊበላ፥ ይኩኖ አምላክ፥ ዓምደ ጽዮን፥ ዘርአ ያዕቆብ፥ በጠቅላላው የጎንደር ነገሥታት ከጥንት ሀገሮች ጋር ያስሰለፉን የኲራታችን ምንጮች ናቸው። የአፄ ቴዎድሮስንና የአፄ ዮሐንስን ቁጡነትና ርኅሩኅነት እናውቃለን፤ ከሥራቸው አይተነዋል፤ ከቃላቸውም ሰምተነዋል። ግን ወድቃ የነበረችውን የዘመነ መሳፍንትን ኢትዮጵያ መልሰው ማቋቋማቸውን እንዴት አድርገን እንረሳለን? “ምነው ወድቃ በቀረች” ከሚል በቀር፥ ሁሉም ባለውለታ ነው። ኢትዮጵያውያንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኩራት ዙፋን ላይ ያስቀመጠውን የአድዋን ድል እንድንነሣ ጦሩን የመሩትን አፄ ምኒልክን እንኳን ያላጠፉትን ያጠፉትንም ቢሆን የማስታወስ ጠባይ ሊኖርብን አይገባም። ኢትዮጵያዊ ውለታቢስ አይደለም። “ኢትዮጵያ ምነው ወድቃ በቀረች” የሚሉ ካሉ፥ አያቶቹን የሚክድ፥ ደማቸውን ደመ ከልብ የሚያደርጉ፥ ራሳቸውን ታሪክ አልባ የሚያደርጉ ናቸው። አለማወቅ ወይም “አባቶቻችን አማራው ባቋቋመው መንግሥት ውስጥ በፈጸሙት ታሪክ ከመኵራት ቢቀርብን ይሻለናል” የሚል ስሜት፥ ከሀገርና ከታሪክ ፍቅር ነፃ አውጥቷቸዋል።

መደምደሚያ፤

አማርኛ ተናጋሪዎችና ሌሎች አገር ወዳድ ተማሪዎች የጫሩትን የዘመናችንን የለውጥ ንቅናቄ ባለሌላ ባህሎች አማሮችን፥ “አብረናችሁ ነን፤ የዲሞክራሲውን ንቅናቄ ግፉበት፤ እንግፋበት” ሲሉ ቆይተው፥ አፋፍ ላይ ሲደርሱ ገፈተሯቸው፤ ከዷቸው፤ ዲሞክራሲን ከዱት፤ የኢትዮጵያን አንድነት ከዱት። ጓደኛንና ሀገርን መክዳትና መካድ የማያሳፍራቸው ሃይማኖተኛ ወገኖች ተወለዱ። “እናንተ ጨቋኞች፥ እኛ ተጨቋኞች ነን፤ ከናንተ ጋር አንድ የሚያደርገን አንዳችም ነገር የለም” የሚል ፈሊጥ አመጡ፤ በዚያው ጸኑበት። “አንድ ሕዝብ ነን” የሚለውን አሳደዱት፤ አንድነታችንን የሚመሰክሩትን ምንጮች ደፈኗቸው፤ ሰነዶቹን አቃጠሏቸው።

አማሮችም በጭቁንነታቸው ላይ ጓደኞቻቸው እነ ሕወሓት (ወያኔዎች) ሲከዷቸውና ሌላ ጭቆና ሲጭኑባቸው፥ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በሀገሪቱ ህልውና ላይ ሲዘምቱባት ሲያዩ፥ “የጭቆና የጭቆና የቀድሞው ጭቆና ይሻለን ነበር፤ የቀድሞ ጨቋኞች ሌላው ቢቀር አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሱለትን የሀገራችንን አንድነት አያስደፍሩም፤ ታሪካችንን አያራክሱም ነበር” ሲሉ ይሰማሉ፤ እኔም ስል እሰማለሁ። ታሪክና ሀገር ህልውናንና ማንነትን ይነካሉ። ስለዚህ ዱርየዎች ታሪካችንን ከታሪካቸው ጋር ሊደመስሱ ሲሞክሩና ሀገራችንን ሲያወድሙ ዝም ብለን አንይ። ትግላችን ምንና ከማን ጋር መሆን እንዳለበት እንወቅ። የምንለው “የዱሮው ይከተት” እንጂ፥ “የዱሮው ይቀጥል” አይደለም። እንደነሱ አለማወቅ ነፃ ያወጣን ሰዎች ስላይደለን፥ የመጀመሪያው ትግላችን “ታሪክ አልባ፥ ማንነት አልባ” ከሚያደርግ ጠላት ጋር ነው። ሀገርን፥ ታሪክን፥ ማንነትን ለማዳን ጥቅመኛ የሆነ ሁሉ፥ አማራ፥ ኦሮሞ፥ ትግሬ፥ ጉራጌ፥ . . . ሳይል፥በሚችለው መንገድና ዘዴ ለመጠቀም መነሣት እንዳለበት ላሳስብ። “ለሀገር የመጣ ነው” የሚለው አነጋገር አያዘናጋን። ለሀገርና በሀገር ላይ የመጣን ያህል የሚያስቆጣና የሚያሳስብ ነገር የለም። አገር ወዳድ ሁሉ የተሳተፈበት የ1888ቱ የአድዋው ድል አድዋ ላይ መደገም ያለበት ጊዜ ከፊታችን ተደቅኗል። ሌሎቹን ጦርነቶች (በረኀብ፥ በድንቁርና፥ በበሽታ፥ በጭቆና ላይ) የምናካሂደው መቆሚያና መቀመጫ ሀገር ሲኖረንና ማንነታችን ሲከበር ነው።