Blog 4. Rule of Law and Governance (in Amharic) by Dr. Getatchew Haile (2013)

መንግሥትና ሕግ አንዱ ያለሌላው የማይኖር የዓይንና የብርሃን ጋብቻዎች ናቸው። ጋብቻው ሕይወታቸው ስለሆነ፥ ብርሃኑ ቢደበዝዝ፥ ወይም ዓይኑ ቢደክም ብርሃኑ ቦግ የሚልበት፥ ዓይኑ የሚጠነክርበት መንገድ ይፈለግላቸዋል እንጂ አይፋቱም። የታሪክ ተመራማሪዎች የሚታመን ማስረጃ እያቀረቡ፥ ኢትዮጵያ የጥንት ሀገር ናት ብለው ሲያሳምኑን፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ባለ ሕግና ባለሥርዓት እንደነበረ መመስከራቸውና ማሳመናቸው ነው። የኢትዮጵያን መንግሥት ጥንታዊነት ተቀብለናል። ከተቀበልን፥ ከዚህ በታች ባሉት ሦስት አርእስት ላይ እንወያይ።

  1. ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ ዘመን የደረሰውን የጥንቲቷን ኢትዮጵያ ሕግ ማን አወጣው?
  2. ሕጉ የግለሰብን መብት ምን ያህል ይጠብቅ ነበር?
  3. ሕዝቡና የሀገሪቱ ባለሥልጣኖች ሕጉን ምን ያህል ያከብሩትና ያስከብሩት ነበር?

መለኮታዊ መንግሥት፤

የኢትዮጵያ መንግሥት፥ እንደማናቸውም የጥንት መንግሥታት፥ መሠረቱ መለኮታዊ ነው። ማስረጃው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችን አምላክ እድሜ ሰጥቶን በሕይወት ደርሰንበታል። ለመለኮታዊ መንግሥት ሕግ አውጪው መለኮት ነው። መጽሐፋችን "ሕግ ይወፅእ እምጽዮን" (ሕግ ከእስራኤላዊት ጽዮን ይወጣል) ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስና በቸሩ ቁርኣን ውስጥ ያሉት ሕግጋት ለዚህ እንደ ማስረጃ ይወሰዳሉ። ሲጀመር፥ መሠረታዊ ሕጎችን አምላክ ለነቢይ ሙሴ በቀጥታ፥ ለነቢይ ሙሐመድ በገብርኤል አማካይነት እንደነገራቸውና በኋላ የተነሡ የክርስትና አባቶች ሲኖዶስንና ፍትሐ ነገሥትን፥ የሙስሊም አባቶች ሸሪዓንንና ሐዲስን እንደ ደነገጉ ተምረናል። መለኮታዊ ሕግ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፥ የአንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉም አንድ ዓይነት ሃይማኖት፥ አንድ ዓይነት መለኮታዊ ሕግ ሲኖረው ነው። ከአገሬው ሕዝብ አንዱ ክፍል ክርስቲያን ሌላው ክፍል ሙስሊም ሲሆን፥ ሕዝቡ በየትኛው መለኮታዊ ሕግ ይተዳደር? ትልቁና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ችግር ይኸ ነበር፤ ምናልባትም ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውን እንደለወጡ ሙስሊሞችም ካልለወጡ በ"ነበር" የሚያልፍ አይመስልም። ንግግሬ ሲቀጥል ምን ማለቴ እንደሆነ ግልጽ ይሆናል።

የኢትዮጵያ መንግሥት መሪ የክርስትናን ሃይማኖት እንዲያከብር ጳጳሱ መጽሐፍ ቅዱስ አስይዞ ያስምለው ነበር። ይኸ ቀርቷል፤ ባይቀርም፥ የሚምለው ሃይማኖቱን እንዲያከብር እንጂ፥ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን የሃይማኖት ነፃነታቸውን እንዲነፍጋቸው አይደለም። ሲነፍጋቸውም አልታየም። ንጉሣዊት ኢትዮጵያ፥ ሙስሊሞች ማንንም ሳይፈሩ በሃይማኖታቸው መሠረት አምላካቸውን የሚያመልኩባት፥ ቤተ ጸሎት (መስጊድ የሚሠሩባት) ሀገር ነበረች። ይኸንን ታሪካችንን የሳዑዲ ታላቁ ሙፍቲ ሸኽ ዐብዱል አዚዝ አል-ሸኽ አሁንም ማርች 16 ቀን 2012 ዓ. እ. "በዐረብ ሰላጤ ያሉ አብያተ ክርስቲያን መፍረስ አለባቸው" ካለው ጋር ስናስተያየው በታሪካችን እንኮራለም። እርግጥ የክርስትና በዓላት በሀገር ደረጃ ሲከበሩ፥ የሙስሊም በዓላት በዚያው ደረጃ አይከበሩም ነበር። መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ሲያሠራ መስጊድ አያሠራም ነበር። በፍርድ ጊዜ ግን መብታቸው ሲነፈጋቸው አልተገኘም፤ የንግድ ሥራውማ አብዛኛውን ጊዜ የነሱ ነበር። በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱትን ክርስቲያኖችንና ወደ መካ የሚሄዱትን ሙስሊሞች ንጉሠ ነገሥቱ እኩል ነበር ከፊታቸው አቅርበው የሚሸኟቸው።

የሀገሪቱ ታሪክ እንደመዘገበው፥ የሰሎሞናዊው መንግሥት የተቋቋመ ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ምድር የሚኖሩ ሙስሊሞች በኢትዮጵያ መንግሥት ስር መሆናቸውን ገጸ በረከት በማምጣት እያሳወቁ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መብት ተሰጥቷቸው ነበር። የግብጹ ሡልጣን ጀቅመቅ በሥልጣኑ ስር የነበሩትን ክርስቲያኖች መጨቆኑን አፄ ዘርአ ያዕቆብ ሲሰማ የጻፈለት ደብዳቤ የኢትዮጵያ ነገሥታትን ርቱዕ ፍትሕ አክባሪነት ያሳያል። የደብዳቤው ፍሬ ነገር "በእኔ ስር የሚተዳደሩ ሙስሊሞች አሉ። የክርስቲያኑን ሕግ እንዲያከብሩ አይገደዱም። ግብር ከመክፈል ሳይቀር ነፃ ናቸው" የሚል ነበር። ማስረጃ ተጨባጭ ምንጭ ለመስጠት ስል የአፄ ዘርአ ያዕቆብን ደብዳቤ ጠቀስኩ እንጂ፥ በክርስቲያን ነገሥታት ዘንድ ርቱዕ ፍትሕ አክባሪነት የተጀመረው በዚያ ጊዜ አይደለም። ክርስትናን የተቀበለው መጀመሪያው ንጉሣችን ዔዛና ለአምላኩ የገባው ቃል፥ "ሕዝቦችን ሳልጨቁን በእውነትና በርትዕ (እገዛለሁ)" ብሎ ነው።

በውይይታችን ርቀን ሳንሄድ በእኛ ዘመን የሆነውን ላስታውሳችሁ እንጂ፥ አልነግራችሁም። ንጉሡ ምንም በመሐላ ቢቀባ፥ ሀገሪቱ የምታከብራቸው ሦስት አርቆ አስተዋይ ሥርዓቶች ነበሯት፤

  1. (1)  በዜጋው ሁሉ ላይ የታወጀ የመንግሥት ሕግና የመንግሥት ፍርድ ቤቶች፤

  2. (2)  የክርስትናን ሃይማኖት በሚመለከት ክርስቲያኑ ሕዝብ የተቀበለው የቤተ ክህነት ሕግና ፍርድ ቤት፤

  3. (3)  የእስልምናን ሃይማኖት በሚመለከት ሙስሊሙ ሕዝብ የተቀበለው የቤተ ኢስላም የሸሪዓ ሕግና ፍርድ ቤት። 

ለወደፊቱም ቢሆን ከዚህ ያማረ መፍትሔ እስኪገኝ፥ በዚሁ መንገድ መሄድ ይሻል ይመስለኛል።
እንዲህ ከሆነ፥ ታዲያ የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች አብሮ መኖር ያስከተለው ችግር ምንድነው? ርእሰ ብሔሩ ሁል ጊዜ ክርስቲያን መሆን አለበት የሚለው በሌሎች ዘንድ ቅሬታን አስከትሎ ነበር። አሁን ቀርቷል። ክርስቲያኖቹ ወደውም ሆነ ተገድደው፥ አስተሳሰባቸውን ለውጠዋል። የዲሞክራሲ አስተዳደርን የተቀበለ ክርስቲያን፥ ሕዝብ የመረጠውን መሪ በሃይማኖቱ ምክንያት አልቀበለውም ሊል አይችልም።

ዋናው ችግር ያለው እሙስሊሞቹ ትውፊት ውስጥ ነው። የሙስሊሞቹ ትውፊት "እስልምና ሃይማኖትና መንግሥት እንጂ ሃይማኖት ብቻ አይደለም" ይላል። በትውፊቱ መሠረት፥ እስልምና የተሟላ ሃይማኖት ሊሆን የሚችለው መንግሥቱ እስላማዊ ሲሆን ነው። ስለዚህ ነገሥታቱ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሆን ያወጁት ሕግ፥ ምንም እንኳ በየትም እስላማዊ መንግሥት የማይደረግ ተራማጅ መፍትሔ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፥ ሙስሊሞቹን አላረካቸውም። ለእነሱ የታያቸውና አማራጭ የሌለው መፍትሔ በትውፊታቸው መሠረት፥ በኢትየጵያ ላይ እስላማዊ አምላካዊ መንግሥት ማቋቋም ነበር።

በአፄ ዓምደ ጽዮን፥ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ፥ በአፄ ልብነ ድንግል፥ በአፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን ያመፁ የአደል (አዳል) ንጉሦች ፍላጎታቸውን ስንመረምረው፥ የክርስቲያኑን መንግሥት ከንጉሠ ነገሥቱ ነጥቆ፥ እንደትውፊታቸው እስላማዊ የፈላጭ ቈራጭ መንግሥት ለማቋቋም ነበር።

ንጉሦቹ መዝመትና ማስገበር ነበረባቸው። ትልቁ ግጭት የተፈጸመው፥ እንደምታውቁት፥ በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ላይ ከግራኝ መሐመድ ጋር ነው። ግራኝ መሐመድ የሚሉት አሕመድ ኢብን ኢብራሂም አል-ጋዚ የሚባለውን ኢማም ነው። ኢማሙ በራሱ ሀገር ሥልጣን ያገኘው፥ የጊዜው ኢማም ለክርስቲያን ንጉሥ መገበሩ አስቆጥቶት እሱን በመገልበጥ ነበር። የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ንጉሣዊ አገዛዝ መቅረቱን እንደፀጋ እያዩ፥ ይኸንን አባቶቻቸው በኢትዮጵያ ላይ ሊያውሉት ሲሞክሩ ብዙ ሕዝብ ያለቀበትን ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ከአእምሯቸው እንደሠረዙት ተስፋ አለኝ።

ታሪካችን ይህ ሆኖ ሳለ፥ የሙስሊሞች ኮሚቴ በሚያዝያ ወር ለዘመኑ ባለሥልጣናት፥ "የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት መላው ህዝባችን በነበረው ምኞት ሁሉም ህዝባችን ታግሏል፣ ብዙዎቹም ለዚህ ዓላማ መስዋዕት ሆነዋል። የዚህ ታላቅ መስዋዕትነት ፍሬዎች አንዱ የሃይማኖት ነፃነት እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ሙስሊምም እምነቱን ያለመሸማቀቅ እና ያለመሸራረፍ ሙሉ በሙሉ እንዲተገብር የሚያስችል እድል አግኝቷል" ሲል የጻፈው፥ የዛሬዎቹን ገዢዎች ልብ ለመማረክ ካልሆነ፥ "የኢትዮጵያ ሙስሊም እምነቱን ያለመሸማቀቅ እና ያለመሸራረፍ ሙሉ በሙሉ እንዲተገብር የሚያስችል እድል" ያጣበት ዘመን አላውቅም። ሆኖም፥ "ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት" ያላቸው ምኞት ከአጋዳይ ትውፊታቸው ለመራቃቸው ቋሚ ማስረጃ ከሆነ እጅ ለጅ ተያይዘን አብረን ለመታገልና አብረን በሰላም ለመኖር እንችላለን። 

ያም ሆነ ይህ፥ የማታ ማታ የበላይ ሕግ የሚሆነው በቊጥር አንድ የተሰጠው ከሕዝብ የመነጨው የመንግሥት ሕግ ነው። እስከዚያ ድረስም ቢሆን ሁለተኛውና ሦስተኛው የሚሠሩት ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በፈቃዱ ለተቀበለው ክፍል ብቻ ነው። ለምሳሌ፥ "በቊርባን ተጋቡ"፥ "ሴቶች ቆንጆ ፊታችሁን ሸፍኑ" የሚለውን ሕግ መቀበል የማይፈልግ እንዲቀበል መገደድ የለበትም። "የዲሞክራሲ ያለህ" እያልን ከምንጮኽበት ምክንያት አንዱ መለኮታዊ አገዛዝ ሊያመጣው ከሚችል ጭቆና ነፃ ለመውጣት መሆኑን ሃይማኖታዊ ሁሉ ልብ እንዲለው ያስፈልጋል።

ሕግ፡ ይወፅእ፡ እምጽዮን፤

አሁን እንግዲህ እንድንወያይባቸው ወደአሰብናቸው ነጥቦች አንድ በአንድ ልግባ። ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከእኛ ዘመን የደረሰው፥ የጥንቲቷ ኢትዮጵያ ሕግ፥ መሠረቱ አምላክ በጣቶቹ ጽፎ ለሙሴ የሰጠው ዓሠርቱ ቃላት ናቸው። ሕግ አውጪውም ገዢውም እግዚአብሔር ነበር። መንግሥቱን ያቋቋሙት ክርስቲያኖች ሆነው ይሁዲነትን አጠንክረው ይዘዋል። ይህም የሚያመለክተው ክርስትናና ሕጉ ኢትዮጵያ የደረሱት፥ ይሁዲነታቸውን አጠንክረው በያዙ የወንጌል ሰባኪዎች መሆኑን ነው። አምላክ ሕጎቹን የሚያስፋፋውና በሥራ ላይ የሚያውላቸው ነቢያት እያለ በሚያስነሣቸው መሪዎች አማካይነት ነበር።

በማህል ቤት እስራኤላውያን እግዚአብሔር የማይወደው ነገር አማራቸው። በአካባቢያቸው ያሉት ሕዝቦች በንጉሥ ሲተዳደሩ አይተው፥ እኛም ንጉሥ እንፈልጋለንና አንዱን ቀባልን ብለው ነቢያቸውን ሳሙኤልን ጠየቁት። ሳሙኤል ፍላጎታቸውን ለእግዚአብሔር ሲነግረው፥ "ያንተን ሳይሆን የኔን ገዥነት ባይፈልጉ ነው" ብሎ ተቆጣ፤ አዘነም። ከቁጣው ሲመለስ፥ ፈቀደላቸው፤ ግን ከዚህ በታች የጠቀስኩትን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፤

"ልብ አርጉ፥ በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ሥርዓት ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገላ ነጂዎችና ፈረስ ጫኞች፥ ለጓሚዎች ያደርጋቸዋል፤ በሰረገሎች ፊትም ይሮጣሉ። ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች የአምሳ አለቆችም (የክብር ዘበኞች) ያደርጋቸዋል። ማሳውን የሚያርሱ፥ ሰብሉን የሚሰበስቡ፥ ፍሬውን የሚለቅሙ (የወረገኑ አገልጋዮች)፥ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹን ዕቃ የሚሠሩ ያደርጋቸዋል። ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቱ ቀማሚና ወጥ ቤቶች፥ ጋጋሪዎችም ያደርጋቸዋል፤ ከእርሻችሁና ከወይናችሁ መልካም መልካሙንም የዘይት ቦታችሁን ወስዶ ለሎሌዎቹ (ለሚንስትሮቹ) ይሰጣቸዋል። ከዘራችሁና ከወይናችሁም ዓሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ የራሱን ሥራ ያሠራቸዋል። ከላሞቻችሁ፣ ከበጎቻችሁ ከፍየሎቻችሁም ዓሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። በዚያች ቀን ራሳችሁ የመረጣሁት ንጉሥ ጭቆና ሲያጠናባችሁ ትጮሃላችሁ፤ በእነዚያም ወራት እግዚአብሔር አይሰማችሁም። ለራሳችሁ ንጉሥ መርጣችኋልና።" 

ይኸም ሆኖ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን ጥሎ አልጣላቸውም፤ የእሱ ምርጥ ሕዝብ መሆንን ኢትዮጵያውያን እስኪወስዱባቸው ድረስ፥ ነገሥታቱን የሚገሥጹ ሕዝቡን ወደ በጎ ሥራ የሚመሩ ነቢያት ይልክላቸው ነበር። ኢትዮጵያውያን የእግዚአብሔር ሕዝብነትን ሲወርሱ ከጽዮን የሚወጣውን ሕግም ተቀበሉ ይባላል። ኢትዮጵያ ክርስትናን ከመቀበሏ በፊት የአይሁድን ሃይማኖት ተቀብላ ነበር የሚለው ባህል በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባያገኝም፥ የጥንቷ ኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ የአይሁድና የክርስቲያን ሕግጋትን ያጣመረ መሆኑ አያጠራጥርም። የብሉይና የሐዲስ ኪዳንን ሕግ ይቀበላሉ። የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን የምናውቀው፥ ብሉያትና ሐዲሳት የሃይማኖት ቅዱሳት መጻሕፍት ሆነው፥ የሕጉ ምንጭ ግን ፍትሐ ነገሥት የሚባለው መጽሐፍ እንደሆነ ነው። ግን ፍትሐ ነገሥት ወደግዕዝ የተተረጐመው አሁን በዓሥራ ሰባተኛው ምእት ዓመት ነው።

እስከዚያ ድረስ የሀገሩ ሕግ ሲኖዶስ የሚባለው መጽሐፍ ነበር። ይዞቱን በአጭሩ ለመናገር፥ ባህላችን እንደሚለው፥ ክርስቶስ ከዐረገ በኋላ ሐዋርያት ተሰብስበው ክርስትናን የተቀበለው ሕዝብ የሚተዳደርበትና እንደ እምነቱ የሚኖርበትን ሕግና ሥርዓት ጻፉ። ተከታዮቻቸው ሊቃውንት እምነትን የሚጋፋ ነገረኛ በተነሣ ቊጥር በጋራ መልስ ለመስጠት እየተሰበሰቡ በዚያው ተጨማሪ ሕጎችና ሥርዓቶች ይወስኑ ነበር። እነዚህ የሐዋርያትና የሊቃውንቱ ውሳኔዎች በአንድነት ተሰብስበው ሲኖዶስ የሚባል መጽሐፍ ወጥቷቸዋል። ቃሉ ሲኖዶስ ስብሰባ ወይም ጉባኤማለት ቢሆንም፥ መጽሐፈ ሲኖዶስ የያዘው የስብሰባዎች መንፈሳዊ ውሳኔዎችን ነው።

የሲኖዶስ ሕግጋት የተጻፉት የግሪክ ቋንቋ የምዕራባውያን ሥልጣኔ መግለጫ በነበረበት ዘመን ስለሆነ በግሪክኛ እንደነበር አያጠራጥርም። በትክክል ያልታወቀው ሲኖዶስ መቸ ወደ ግዕዝ እንደተመለሰ ነው። ሆኖም፥ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የተደረሱ ጽሑፎች ሲጠቅሱት ተገኝተዋል። ይህ ሐቅ የሚመሰክረው፥ የጥንቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋቋመው ፈሪሀ እግዚአብሔር በሚገለጽባቸው ሕግጋት ላይ እንጂ፥ ነፍጠኞች ሕዝቡን እንደፈለጉ የሚበዘብዙበት ሥርዓት እንዳልነበረ ነው።

በኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው መርጦ ባለሙሉ ሥልጣን ንጉሥ አድርጎ የሚሾመው፥ እንዲወክለውና በእሱ ስምና እሱ በሰጠው ሕግ ሕዝቡን እንዲያስተዳድር ነው። አንድ ጊዜ፥ አፄ ዘርአ ያዕቆብ ስለሰጠው ፍርድ ሲጽፍ፥ "ይኸን ያደረግሁት ለፈጠረኝና ለአነገሠኝ የመንጋው እረኛ ላደረገኝ ለእግዚአብሔር አምልኮት ቀንቼ ነው። እግዚአብሔር የናንተ (የካህናቱ) እና የመንጋው እረኛ አድርጎ ሾሞናል" ያለው በዚህ እምነት ነው። ለመንገሥ በእግዚአብሔር ስም የተቀባውን ማንም እንዳይነካው የደረሰን መንፈሳዊው ሕግ፥ "በእግዚአብሔር ቅቡ ላይ እጅህን አታንሣ" 

ይላል። ለንጉሡ የማይገሠሥ ሙሉሥልጣን ሰጥቶታል። ሆኖም፥ ማስታወስ ያለብን ሙሉ ሥልጣን የሰጠው ሕዝብ የሚበድሉ ወንጀለኞችን በትክክለኛ ፍርድ እንዲቀጣ እንጂ፥ ሥልጣኑን ለግል ጥቅሙ እንዲያውለው አይደለም። ሥልጣን የሰጠሁትን አትድፈሩ ማለቱ፥ "ሹሜን መድፈር እኔን መድፈር ነው" ማለቱ እንደሆነ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ባስነሣላቸው በነቢዩ ሳሙኤል ምትክ ንጉሥ ሲፈልጉ ለሳሙኤል የነገረው ያስረዳል፤ "አንተን ሳይሆን በእነሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን መናቃቸው ነው" ብሎት ነበር። በእግዚአብሔር ስም የተቀባ ንጉሥ ሕገ ወጥ ሲሆንና ሥልጣኑን ለግል ጥቅሙ ሲያውል፥ ሕጉ መምዕላይ ብሎ ይኰንነዋል። (አደራ-በላ) አመፀኛ ማለት ነው።

ሕዝባችን በይበልጥ የሚያውቀው ስለ ክብረ ነገሥት ነው። ግን ለክብረ ነገሥት ትልቅ ቦታ የተሰጠው ለምን እንደሆነ የሚያውቅ አይመስለኝም። የታሪኩ አስኳል ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሲሆን፥ ታቦተ ጽዮን የሚሉት ዓሠርቱ ቃላት የተቀረጹበትን የሕግ ሰሌዳ ነው። በየቤተ ክርስቲያኑ ያሉት ታቦታት ከፍ ያለ ክብር የሚሰጣቸው ደግሞ ዓሠርቱ ሕግጋት ያሉበት የታቦተ ጽዮን አምሳያ ስለሆኑ ነው። እንዲህ ከሆነ፥ ኢትዮጵያውያንን "ታቦት ያመልካሉ" ብሎ ከማማት ይልቅ "ሕግ ያከብራሉ" ቢባል እውነትነት ይኖረዋል። አንድን በደለኛ ለማቆም "በሕግ አምላክ" የምንለው ሕግ የሚፈራ አምላክ እንዳለው ሁሉም ስለሚያውቅ ነው። የኢትዮጵያ ንጉሣዊ መንግሥትና ሕዝቡ ሕግን የሚያከብሩት እንደዚህ በከፍተኛ ደረጃ ነበር።

ሰነዶቹ እንደሚመሰክሩት፥ ነገሥታቱን ከሚያጅቡት ባለሥልጣናት ማህል ትልቁን የክብር ቦታ የሚይዙት ሕግ ዐዋቂዎችና ዳኞች ነበሩ። ለምሳሌ፥ ነገሥታቱ ርስት ለገዳማት ሲጐልቱ፥ በሃይማኖት ጭቅጭቅ ጊዜ ዳኝነት ሲቀመጡ፥ በዓላት ሲያከብሩ፥ ከመኳንንቱ ጋር ለምስክርነትና ሕግ ለመጥቀስ ሕግ ዓዋቂ ታላላቅ ሰዎች በቦታው ይገኛሉ። ነገሥታቱ ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ በሕግ ዓዋቂ ታላላቅ ሰዎች መታጀባቸው ለሕግ የቱን አክብሮት እንደነበራቸው ያሳያል። በዕለቱ የተመዘገበው ሰነድ ሲመረምር እዝርዝሩ ውስጥ ሁል ጊዜ ዳኞችና ሕግ ዐዋቂዎች አሉበት። የፍርድ ጒዳይ ከንጉሡ ችሎት ሲደርስ ንጉሡ ብቻውን አይፈርድም። ከችሎት ላይ የሚቀመጡ መኳንንትና ሊቃውንት የክብር ተራቸውን ጠብቀው ከታች ወደላይ ይፈርዳሉ። ንጉሡ ሁሉን አዳምጦ የማይሻረውን የመጨረሻውን ፍርድ ይሰጣል። "አለቀ፥ ደቀቀ" ይባላል። ይህ አባባል አማርኛ ውስጥ የገባው ከንጉሡ ችሎት ተነሥቶ ነው።

ነገሥታቱ የሕዝብን ጥቅም ይጠብቁ እንደነበረ ለማሳየት አንድ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቤተ መንግሥት የሆነ ነገር ላንሣ፤ የዚያ ጊዜ ቢትወደድና የገኒ ንጉሥ ኢሳይያስ ይባል ነበር። ከንጉሡ ዘንድ ቀርቦ፥ "እነዚህ ሹመቶች አይበቁኝም፤ በነሱ ላይ የጎጃም ንጉሥነትን ደርብልኝ" አለው። ንጉሡም፥ "ቢትወደድ ከሆንክ እዚሁ በመንግሥቱ አደባባይ መገኘት ይኖርብሃል። ታዲያ እዚህ ሆነህ ጎጃምን እንዴት በፍትሕ ልትገዛ ትችላለህ? እዚህ ባለህበት ጊዜ የጎጃም ሕዝብ ቢበደል፥ አምላክ ደሙን ከማን ይቀበል ይመስልሃል? ከእኔ አይደለምን?" ብሎ ሸኘው። የገዢዎቹ ሃይማኖተኛነት ጭካኔያቸውን ለመቆጣጠር ከዲሞክራሲ የበለጠ ኀይል አለው። ሕግን ከሚፈራ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሳይሻል አይቀርም። በአንድ ዘመን ንጉሡ ይሙት በቃ የፈረደበትን ሰው እንዲምረው ሽማግሌዎች ቢለምኑት እምቢ ብሎ ነበር። ድንገት በዚያው ጊዜ ፀሐይ ብርሃኗን ነፈገች። (solar ecliple) ይህ የሆነው በእሱ እምቢተኝነት መሆኑን ያመኑ ንጉሡን ስላሳመኑት፥ ይሙት በቃ የፈረደበትን እስረኛ ነፃ ለቀቀው። ትልቁ ችግር ነገሥታቱ ፍጹም ጻድቃን ሲሆኑ፥ ወይ መንፈሳዊነቱ ላይ ብቻ ያተኲራሉ፤ ወይም ገዳም ገብተው ይመነኲሳሉ።

አፄ ዘርአ ያዕቆብ ንጉሥን በግላጭ ለሚገሥጽ ሲኖዶስ ታላቅ አክብሮት ነበረው። የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ያደሰው፥ ሕዝበ ክርስቲያኑንም ያስተዳደረው ሲኖዶሱ ውስጥ ባሉት ሕግጋት ነው። ኢየሩሳሌም ላለው ገዳማችን የላከው ታላቅ ስጦታ የሲኖዶስ ቅጂ ነበር።

ፍትሐ፡ ነገሥት፥

ከዓሥራ ሰባተኛው ምእት ዓመት ጀምሮ እስከ ሃያኛው ምእት ዓመት ድረስ የሃገሪቱ መተዳደሪያ ሕግ ፍትሐ ነገሥት ነበር። ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊና ፍትሕ ሥጋዊ የሚባሉ ሁለት ክፍል አሉት። ስሞቹ እንደሚያመለክቱት፥ የመጀመሪያው ስለቤተ ክህነት፥ ሁለተኛው ስለቤተ መንግሥት ነው። ሁለተኛው ክፍል፥ "በሀገራችሁ በሰዎች ላይ በፍርድ ጊዜ ቀጥተኛውን ፍርድ ሳያጣምሙ፥ ፊት አይተው፥ ጉቦ በልተው ሳያዳሉ እንዲፈርዱ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ዳኞች ሹሙ። ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ሳይቀር እውነትን እንዳያይ ያሳውርና ትክክሉን ቃል ያስለውጣል" የሚለውን መንደርደሪያ ከኦሪት በመጥቀስ ይጀምራል።

ስለ ንጉሥ ሲናገር፥ "ከዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ፥ በእድሜ ልኩ አብሮት የሚኖር አምላካዊ ጽሑፍ ካህናት ይጻፉለት፥ ያንን እያነበበ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማርና ትእዛዞቹን እንዲያከብር" ይልና፥ "በመንጋው ላይ በትክክል ይፍረድ፤ ለራሱም ሆነ ለሌሎች፥ ለልጆቹም ሆነ ለዘመዶቹ፥ ወይም ለባዳ አያዳላ" ይላል። በሕጉ መሠረት፥ ንጉሡ ጦርነት ሲያውጅ የሚከተለው ሠራዊት በፈቃዱ እንጂ በግድ አይደለም። ጠላት እንዲያሸንፍ የሚያጋልጥ፥ የተመከረውን ምክራችሁን የሚያወጣ፥ ወይም ወደነሱ ሄዶ መሣሪያ የሚሸጥላቸው ይሰቀል፤ ይቃጠልም" ይላል። ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል እንደ ታጠቀው እንደ ሻዕቢያ ያለ ጠላት ጋር የዶለተ ማለት ነው። ሊሰቀሉ የሚገባቸው ሰቃሊዎች ሆነዋል።

የሕግ አክብሮት የተጣሰው የኢትዮጵያ መንግሥት አንድነት ተጥሶ ዘመኑ ዘመነ መሳፍንት በሆነበት ጊዜ ነው። የጎንደር ቤተ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ወግና ሥርዓት በጥንቃቄ ስለተመዘገበ፥ ከዚያ በፊት የዜጎች መብት እንዴት ይከበር እንደነበረ፥ መዝገቡን እየቀዱ ማሳየት ይቻላል። የሕዝብ መብት እንደ ታቦት ይከበር እንደነበረ፥ ሥልጣኔያችንም የረቀቀ እንደነበረ ለማሳየት በግዕዝ የደረሰንን ሰነድ ወደአማርኛ እየተረጐምኩ ላቅርብ፤ 

ግራና ቀኝ ወምበሮች ለፍርድ በችሎት ሊቀመጡ ሲሉ፥ መጀመሪያ በቅዱስ ያሬድ ቃል በዜማ እንዲህ ብለው ይጸልያሉ፤ "ሃሌ ሉያ፤ ዕዳ በሚከፈልባት በዚያች ዕለት፥ ፍርድ በሚሰጥባት በዚያች ዕለት፥ በዚያች በእግዚአብሔር ዕለት ነፍሳችንን ምን እንላታለን? . . ." ይኸንን ጸሎት ሦስት ጊዜ እስከመጨረሻው ይሉና ትርጓሜውን ከጽራግ ማሠሬ (ከንጉሥ አልባሽ) እና ከሊቀ ማእምራን (ከትልቁ ሊቅ) ይሰማሉ። ከዚያ በኋላ (ዳኞቹ) በንጉሥ ሰቀላ ቤት ለፍርድ በቀኝና በግራ ይቀመጣሉ። ከበሽተኞች፥ ከሴቶች፥ ከመምህራን በቀር ትንሹም ትልቁም ሹምም ብሕትወደድም ደጃዝማችም ተቀምጦ አይፋረድም። ቁጭ ብሎ የሚፋረድ ባለሥልጣን የአክሱም ነብርድ ብቻ ናቸው። 

ትርጓሜ ማለት በግዕዝ የተነበበውን እንደዚህ እኔ ወደ አማርኛ እንደተረጐምኩት ጥሬ ትርጒም ማለት አይደለም። የምጽአት ዕለት ነፍስ በታላቁ ዳኛ ፊት ቆማ፥ እያንዳንዱ ሰው የሠራው ሥራ በጎውና ክፉው ይመዘናል። የሰውየው የዘላለም ሕይወት የሚወሰነው በሚመዘነው ሥራ ነው። ሚዛኑን የሚይዙት መላእክት ስለሆኑ፥ ተዳላብኝ የሚል አይኖርም። ማንም ሰው ወደፈለገበት ሕይወት ለመሄድ ዕድሉ አሁን እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስረዷቸዋል። ለዳኞቹ በተለየ የሚጠቅሱላቸው፥ "እንዳይፈረድባችሁ በአድላዊነት አትፍረዱ" የሚለውን የክርስቶስ ቃል ነው። አባ አበክረዙን የሚባሉ መነኲሴ የገዳማቸው አለቃ (አበ-ምኔት) እንዲሆኑ ሲጠየቁ፥ እምቢ ለማለት፥ "እርጉሞች ሆይ፥ ወዲያ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደተዘጋጀው እሳት ሂዱ" የሚለውን የጌታ ቃል ጠቅሰው፥ ከዚህ ቃል "በቀር ሰውን እንደማዘዝ የሚያስፈራኝ ሌላ ነገር የለም" ማለታቸው የዕለተ እግዚአብሔርን አስፈሪነት በማስታወስ ነው። ከድርሰቶቻቸው እንደምገምተው፥ አባቶቻችንና እናቶቻችን እግዚአብሔን ያከብራሉ፤ ፍርዱንም እንደማይስት ተወርዋሪ ጦር ይፈሩ ነበር።

በእኛ ዘመን እንኳ የሆነውን ብናስታውስ፥ የበደለ ሰው፥ "በንጉሥ አምላክ፥ በሕግ አምላክ፤ አትሂድ" ከተባለ፥ ሁለቱ ተያይዘው ከዳኛ ዘንድ ይሄዳሉ እንጂ፥ የንጉሥና የሕግ አምላክ ስም ሲጠራ፥ ደፍሮ አይሄድም። የመንግሥት ዳኛ በአካባቢው ከጠፋ ዳኛ አቁመው ይፋረዳሉ። ሌላው ትልቁ ባህላችን ሽምግልና ነው። የሕዝቡ እምነት አሁንም እንደጸና ነው። ትልቅ ችግር የተፈጠረው የማርክሲስት ፍልስፍና የወጣቱን እምነት ስላናጋው ነው። እንደነ መለስ ያሉ ልጆች ከቤተ መቅደስ ገብተው ሲጃራ ከማጉ፥ የሰውን ሕይወት ከትንኝ ሕይወት በላይ ለማክበር ምንም ምክንያት አይኖራቸውም፤ አልነበራቸውምም። ሰው ቢሞት ምናለበት የሚሉና የሰውን ሕይወት ሲያጠፉ ምንም የማይቆረቁራቸው ከሓዲዎች የሚጽፉትን ሕግ አምላክን የሚፈሩ ነገሥታት ከሚገዙበት ሕግ ጋር ማስተያየት ብርሃንን ከጭለማ ጋር እንደማስተያየት ይቈጠራል።

የሰው ልጅ ሌላውን እንዳይበድል የሚቆጣጠረው፥ አንደኛ፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር፥ ሁለተኛ፥ በትምህርት የዳበረ የተፈጥሮ ርኅራኄው፥ ሦስተኛ፥ የመንግሥት የጸጥታ ኀይል፥ አራተኛ፥ የተደራጀ የሕዝብ ኀይል ናቸው። እንደነ መለስ ያሉ ሽፍቶች እግዚአብሔር የለም ካሉ፥ ርኅራኄያቸው ሳይለመልም ገና ከእንጪጩ ከተጨናገፈ፥ የጸጥታው ኀይል በእጃቸው ከሆኑ፥ ከአራቱ ውስጥ ሊሆን የሚችለው አንዱ ብቻ ነው፤ የሚፈሩት የሚያንቀጠቅጣቸው አንድ ድርጅት ማቋቋም። ይህ ግዴታ እኛ ላይ ወድቋል። ግዴታችንን ተቀብለን የሚፈሩት ድርጅት ካላቋቋምን፥ ቀን የጐደለበትን ሁሉ አስሰልፈው፥ ሕግ አክባሪ፥ እግዚአብሔርን ፈሪ የነበረውን ሕዝብና ገናና ታሪኩን ሲረግሙና ሲረግጡ፣ ሲቦዘቡዙትም ይኖራሉ። የሚፈሩት ድርጅት ካላቋቋምን፥ ታሪክ እኛን ዳተኞቹንም ከእነሱ እኩል ይወቅሰናል።